News detail

Image Here

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለይም ዩኒቭርሲቲዎች የአየር ንብረት ለወጥን ለመከላከል አይተኬ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባቸው ገለፀ። የካቲት 29/2017 ዓ.ም (ፕ.ል.ሚ. - አ/አበባ)

ዩኒቨርሲቲዎች ኢትዮጵያ የጀመረችውን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ውስጥ የማይተካ ሚናቸውን እንዲወጡ የፕላንና ልማት ሚንስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ፍጹም አሰፋ አሳሰቡ።

ክብርት ሚኒስትሯ ይህን ያሳሰቡት ዛሬ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ራስ መኮነን አዳራሽ በተካሄደው 'የኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች የአየር ንብረት ለውጥ ፎረም ምስረታ እና የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ ስነ-ስርዓት' መድረክ ላይ በመገኘት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው።

ዩኒቨርሲቲዎቻችን እያጋጠመን ያለውን ችግር መፍታት የሚያሰችል ከመንግስት በተለይም ከፖሊሲ አውጪው ጋር በቅርበት እና ችግሩን በአግባቡ ተገንዝቦ መረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ቀረጻ አና ዝግጅት ላይ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ክብርት ሚኒስቴሯ ገልጸዋል። "የዩኒቨርሲቲዎችን ሚና ማንም ሊተካው የማይችለው እና የሁሉ ችግር መፍቻ ቁልፍ መጀመሪያ ነው።" ነውም ብለዋል።

ይህን የማይተካ ሚናቸውን በማሳደግ ስኬታማ ውጤት ለማስመዝገብ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የአየር ንብረት ለውጥ ፎረም ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል። በዚሁ መሠረት ዩንቨርስቲዎቹን በአጀንዳው ዙሪያ የሚያስተሳስር ፎረም በመድረኩ ተመስርቷል። “የኢትዮጵያ ዩኒቭርሲቲዎች የአየር ንብረት ለውጥ ፎረም” የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በሰብሳቢነት ትምህርት ሚኒስቴርና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በምክትል ሰብሳቢነት የሚመሩት ሲሆን ስምምነቱን ከፈረሙት የፎረሙ 47 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጠቅላላ ጉባኤ አባላት መካከል 13 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መመረጣቸውን በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡ የመግባቢያ ሰነዱንም ክብርት ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ከሁሉም የዩንቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች እና ተወካዮች ጋር ተፈራርመዋል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ስዩም መኮነን የአየር ንብረት ለውጥ በአንድ ተቋም ብቻ ምላሽ ስለማያገኝ የብዙ ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል። ኢትዮጵያ የጀመረችው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ውስጥ ዩንቨርስቲዎች በጥናት እና ምርምር እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል። ዩኒቨርስቲዎች በእውቀት ላይ የተመሠረተ የአየር ንብረት ፋይናንስ ማፈላለግ ላይም ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።

ከትምህርት ሚኒስቴር የመጡት እና መልዕክት ያስተላለፉት ዶ/ር ኤባ ሚጀና በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያሉ ችግሮች እጅግ የተወሳሰቡና የሚያስከትሏቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተፅእኖዎች ቀላል እንዳልሆነ ጠቁመው በዚህ ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚገናኘውን ግብ 13 የአየር ንብረት ለውጥና ተፅእኖዎቹን ለመዋጋት አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ የሚለውን ወደ ተግባር መተርጎም ላይ ጉልህ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የዩኒቨርስቲ ምሁራን፣ መንግስትና የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት እንዴት ተቀራርበው ይስሩ በሚል መነሻ ሰነድ በፕሮፌሰር በላይ ስማዕነ - ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቀርቦ ወይይት ተደርጎበታል።

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ሥራዎችን አካታችና አሳታፊ ለማድረግ ብሎም ያስቀመጣቸውን ስትራቴጂክ ግቦችን ለማሳካት ከዋና ዋና ባለድርሻ አካላት ጋር ከግሉ ዘርፍ ጭምር ተከታታይ ውይይቶችን እያደረገና ቅንጅታዊ አሠራሮችን በከፍተኛ ደረጃ በመዘርጋት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።

recent News
  • Image Here

    በፕላንና ልማት ሚንስቴርና ተጠሪ ተቋማት በአማራ ክልል ለተከናወነው …

    14 March 2025
  • Image Here

    በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የፋይናንስ ተቋማት አየር ንብረት …

    13 March 2025
  • Image Here

    የዘላቂ ልማት ግቦችን ተግባራዊነት ለማጠናከር ባለሙያዎች ተቀናጅተው ሊሰሩ …

    13 March 2025