የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ግምገማ ተደርጎባቸዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም፣ የሃብት አጠቃቀምና የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም የቁልፍ ውጤት አመላካች የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቶችን አቅርበዋል።
ክብርት ሚኒስትሯ በሪፖርታቸ በሰው ሃብት ልማት፣ በልማት ዕቅድና በመንግስት ኢንቨስትመንት፣ በተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ የመገንባት እና ተያያዥ የዕቅድ አፈፃፀምን አመላክተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አስተማማኝ ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደት ስኬታማ የሆኑ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በፖሊሲና ስትራቴጂ ማዕቀፍ የማሻሻልና ዝግጅት ስራም የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና የሚኖረው የካርቦን ንግድ ፖሊሲ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የሕግ ማዕቀፉ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባም በፓሪሱ ስምምነት አንቀጽ-6 መሰረት በኮፕ-29 በአዘርባጃን ባኩ በተደረገው ስብሰባ መነሻነት ኢትዮጵያን በካርቦን ንግድ ተጠቃሚ እንድትሆን ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች የተመዘገቡት ስኬቶች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የታቀደለትን ከ8.4 በመቶ በላይ ማሳካት እንደሚችል አመላካች መሆኑን ሚንስትር ክብርት ዶ/ር ፍጹም አሰፋ አስታውቀዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ምላሽና ማብራሪያ ይሻሉ ያሏቸውን ጥያቄና አስተያየቶች በጽሁፍ አቅርበው የፕላንና ልማት ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል በሁሉም መስክ ተቋማዊ የማስፈጸም አቅምን በማጎልበት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ በትኩረት እየሰሩ እንዳሉ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጿል።