የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፤ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት፤ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት እንዲሁም የኢትዮጵያ አከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በ2017 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ በዛሬው ዕለት የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር በለጠ ሞላ በውይይት መድረኩ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት የእቅድ አፈፃፀም የውይይት መድረኩ በካቢኔ ደረጃ ከተካሄደው የቀጠለና በየደረጃው ሰራተኛውም በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ እንዲመክርበት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው አሁን ላይ ያለውን ዓለምቀፍ አንድምታ ለሀገራችን የሚኖረውን ጥቅምና ጉዳት ብሎም የጋራ ውጤትን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሀገሪቷ ራዕይ ጋር በማስተሳሰር የሚታይበት ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የስልጣን ርክክብ ከተደረገ በኋላ የለውጡ መንግስት የመጀመሪያው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርምን ጨምሮ በርካታ ሪፎርሞችን ሲያካሄድ መቆየቱን የገለፁት ዶክተር በለጠ አሁን የምንገኝበትን በማወቅ ቀጥሎ የምንሄድበትን ከማቀድ በተጨማሪ የተመዘገቡ ውጤቶች የሚዘከርበት፤ መድረክ በመሆኑ የአመራሩና የሰራተኛው ተሳትፎ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በረከት ፍስሃፅዮን የአለም አቀፍ የኢኮኖሚ አዝማሚያ ለኢትዮጵያ ያለው አንደምታ፤ በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም አፈፃፀም ውጤቶችና አዝማሚያዎች፤ በመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም፤ በዘላቂ ልማት፣ በማህበራዊ አካታችነት እና በሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ለአይበገሬነት እንዲሁም አስቻይ ሁኔታ ለዘላቂ ልማት፣ በሰላም፤ ለዲፕሎማሲ እና ትብብር ነጥቦች ላይ የእቅድ አፈፃፀሞችን አቅርበዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም እንደ ተቋም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን እና የተጠሪ ተቋማትን የዘርፍ አፈፃፀም ሪፖርት እና በቀጣይ በሀገር ደረጃ እና በዘርፍ ደረጃ ትኩረት ስለሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ለታሳታፊው አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም በመድረኩ ከቀረበው የ2017 ዓ.ም የሶስተኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ በመመርኮዝ የቀጣይ ሶስት ወራት ተግባራትን በተሻለ ደረጃ እና በውጤት ቀሪ ተግባራትን ለማስመዝገብ የሁሉም ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ሃላፊነት ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በውይይት መድረኩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና የተጠሪ ተቋማት ሚኒስቴር ዴኤታዎች፤ አመራሮች፣ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡