ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመግታት ጠንካራና ቀጣይነት ያላቸውን እርምጃዎች እየወሰደች መሆኑ የኢፌዴሪ ፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህ የተባለው የመጀመሪያ መድረክ በሆነው ብሔራዊ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅድ (NDC.3) በተመለከተ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተለያዩ የባለድርሻና የልማት አጋር ድርጅቶች ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው።
በውይይት መድረኩ ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ስዩም መኮንን ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በተፈጥሮ ሀብት ጸጋ የታደለች ብትሆንም የአየር ንብረት ለውጥ ሀገሪቱ በምታከናውናቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስራዎች ላይ ጫናዎችን እያደረሰባት ይገኛል ብለዋል።
ኢትዮጵያም ይህን ተጽዕኖ ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች፤ ነገር ግን የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል የብዙ ባለድርሻ አካላትን ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ አለማቀፍ ፣ አህጉር አቀፍና ሀገር አቀፍ የልማት ተቋማት ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል የፋይናንስ ተግዳሮት በመኖሩ ባለድርሻና ለጋሽ ድርጅቶች የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በኢትዮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ተወካይ ሳሙኤል ዶይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ትክክለኛው መንግድ ላይ ትገኛለች ብለዋል። ድርጅታቸውም ከሌሎች ባለድረሻ አካላት ጋር በመሆን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎችን ከፓሪስ ስምምነት ጋር በማጣጣም ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአለም የተፈጥሮ ሃብት ኢንስቲትዩት (World Resource Institute-WRI) ተወካይ አክሊሉ ፍቅረስላሴ (ዶ/ር) ናቸው።
"ኢትዮጵያ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ እቅድ (NDC.3.0) በመተግበር ግንባር ቀደም አገር ነች" ብለዋል።
የNDCP አገር አቀፍ ማካተት ልዩ ባለሙያ የሆኑት ግሎሪያ ናማዚ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የመሬት አያያዝ (sustainable land management)፣ አገር በቀል ኢኮኖሚና አነስተኛ የጋዝ ልቀት ላይ በትጋት እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለምትተገብረው በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ እቅድ የNDC 3.0 ዝግጅት አጠቃላይ እቅድና ሂደት (Developing and Invetstable NDC3.0) ላይ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲና ስትራቴጂ ትንተና እና አካቶ ትግበራ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሆኑት አባስ መሃመድ እንዲሁም በዶ/ር ሙክታር አብዱኬ ጽሐፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በዳሰሳ ጽሑፋቸውም በእስካሁን አፈፃፀሞች የተለዩ ተግዳሮቶችንና የአዲሱን እቅድና የማስፈፀሚያ ስልቶቹን በጥልቀት አቅርበዋል።
የዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራምና ሌሎች የልማት ድርጅቶች ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የአየር ንብር ለወጥ መከላከል እና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል